Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመች።
የመግባቢያ ሥምምነቱን የውኃና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ ከደቡብ ሱዳን የውኃና ግድብ ሚኒስትር ፒተር ማርሴሎ ጋር ተፈራርመዋል።
ሁለቱ አገራት ከፖለቲካዊ አጋርነት ባለፈ በምጣኔ ሀብት ረገድም ትስስራቸውን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑ በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን በመጀመሪያ ዙር 100 ሜጋ ዋት ኃይል የምታቀርብ ሲሆን÷ በሂደት ደግሞ መሰረተ ልማትን በማጠናከር የሽያጭ መጠኑን በየደረጃው ወደ 400 ሜጋ ዋት ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በሥምምነቱ መሰረት የጥናት ሥራዎች በቅድሚያ የሚከናወን ሲሆን÷ በቀጣይ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን በሁለቱ አገራት መንግሥታት በኩል በማከናወን ከሦስት ዓመት በኋላ ኃይሉን ወደ አገሪቱ ተደራሽ በማድረግ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዷል።
የኃይል ማስተላለፊያ ሥፍራዎች የአዋጭነት ጥናት በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራው ይጀመራል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.