Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 8 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ 8 ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የጤና መሰረተ ልማት ዳይሬክተር ኢንጂነር ታደሰ የማነ እንደገለጹት÷ መንግሥት የሕዝቡን መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።
ይህን ተከትሎም የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የህክምና ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ደግሞ በስፋት ሊከሰቱ የሚችሉ የድንገተኛና ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ባለ 11 ወለል ሕንጻ ያለው ሁሉን አቀፍ ሆስፒታል ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ለግንባታውም 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር መመደቡን ነው የገለጹት፡፡
ጎን ለጎንም በ550 ሚሊየን ብር ወጪ ሁሉን አቀፍ ህንጻ የሚገነባ ሲሆን÷ በውስጡ የህክምና መስጫ ማዕከላት፣ ላቦራቶሪዎችና የምርምር ማዕከላት እንደሚገኝበት ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የደም ናሙና ምርመራና የሲቲ ስካን የመሳሰሉ ውስብስብ ምርመራዎች የሚካሄዱበት ትልቅ የምርመራ ማዕከል በ800 ሚሊየን ብር ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።
በአዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚገነባው ለዚሁ የጤና ማዕከል÷ ዲዛይን ተዘጋጅቶ፣ የጨረታው ሂደት ተጠናቆ ግንባታ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተጓዳኝም ከቆዳና ቆዳ ነክ ችግሮች ጋር ያለውን ሰፊ የጤና ችግር በዘመናዊ መንገድ ሊያቃልል የሚችል የህክምና ማዕከል ግንባታ በቅርቡ በ2 ቢሊየን ብር ወጪ ይጀመራልም ነው ያሉት።
ከእነዚህ ግንባታዎች በተጨማሪ ከዓለም ባንክ ከተገኘ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ የሁለት ህክምና ተቋማት ግንባታ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው÷አንደኛው በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ይሆናል የተባለ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ማዕከል ሲሆን የጨረታ ሂደቱ እየተጠናቀቀ መሆኑንም አመላክተዋል።
በበጀት እጥረት ሥራው ቆሞ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክትም ከባንኩ በተገኘ 1 ቢሊየን ብር ድጋፍ ግንባታውን የማስቀጠል ሥራ እንደሚከናወን ነው የገለጹት።
በማስፋፊያ ግንባታው ደረጃቸውን የጠበቁ የመድኃኒት ማከማቻና ማቀዝቀዣ መጋዘኖች የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎችና በርከት ያሉ ተሽከርካሪዎችን ሊያስተናግድ የሚችል የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።
ሁሉንም ፕሮጀክቶች በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱንም ኢንጂነር ታደሰ አረጋግጠዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.