Fana: At a Speed of Life!

አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ሩቅ ምስራቅ ሳለን ጃፓኗን ወድጄ” በሚል እውነተኛ ታሪካቸው የተዘፈነላቸውና የባለብዙ ታሪክ ባለቤቱ አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
አርቲስት 50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ ብሩ በሰሜን ሸዋ ቡልጋ አውራጃ በ1926 ተወለዱ፡፡ ከዛም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እድገታቸውና የልጅነት ጊዜያቸውን ላምበረት ሾላ አካባቢ አሳልፈዋል፡፡
በ1940 ዓ.ም የክብር ዘበኛ ሰራዊትን በመቀላቀል ከሁለት አመት ቆይታ በኋላ በ1943 ዓ.ም የአንደኛው ቃኘው ሻለቃ እንዲሁም በ1946 ዓ.ም ከአራተኛው ቃኘው ሻለቃ ጋር ወደ ኮሪያ ዘምተዋል፡፡
ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላም ለፈጸሙት ወታደራዊ ግዳጅ የቀዳማዊ ይለስላሴ የጦር ሜዳ የወርቅና የብር ሜዳልያ፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኮሪያ ጦርነት መታሰቢያ፣ የዳግማዊ ሚኒሊክ የጦር ሜዳ የወርቅ ሜዳልያ፣ የቀዳማዊ ይለስላሴ የክብር ሜዳልያ፣ የክብር አምባሳደር የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም ከኮሪያ እና አሜሪካ መንግስታት የተመድ ሳኒቴሽን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ከዚህ ባለፈም የ25 አመት የረጅም አገልግሎት የወርቅ ሜዳልያ፣ የ15 አመት አገልግሎት የብር ሜዳልያ እነዲሁም የተዋጊ ምልክት የደረት አርማ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።
በ1949 ዓ.ም ወደ ሙዚቃና ቴአትር ክፍል በመዛወር ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
50 ዓለቃ ሸዋንዳኝ ወልደየስ በ1954 ዓ.ም ከወይዘሮ የሽመቤት ወለደማሪያም ጋር ትዳር መስርተው 8 ወንዶችና 3 ሴቶች በድምሩ 11 ልጆችን አፍርተዋል፤14 የልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
በ1974 ዓ.ም ከክብር ዘበኛ ሙዚቃ ኦርኬስትራ ጡረታ ከወጡ በኋላ በግላቸው የራሳቸውን ስራ እየሰሩ ህይወታቸውን ሲመሩ ቆይተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.