Fana: At a Speed of Life!

በጅቡቲ የሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽህፈት ቤት ህንጻ እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጅቡቲ የሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽ/ቤት ህንጻ እድሳት ተጠናቆ ተመረቀ፡፡

የገንዘብ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ፣ አምባሳደር ብርቱካን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም በጅቡቲ የሚገኙ የኢትዮጵያ ተቋማት ተወካዮች እና የኮሚዩኒት አባላት በተገኙበት የቀድሞ የኢፌ.ዲሪ ኤምባሲ ጽ/ቤት ህንጻ እድሳት ምርቃት መርሐ ግብር ተካሂዷል።
አቶ አህመድ ሽዴ በጅቡቲ የኢፌዴሪ ኤምባሲን እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የህንጻ እድሳት ፕሮጀክቱን በመልካም ሁኔታ ማጠናቀቃቸውን ጠቅሰው ፥ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ቡርቱካን አያኖ እድሳቱ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ መጠናቀቁን ገልጸው ፥ ሌሎች ሚሲዮኖችም ይህንኑ ተሞክሮ ሊጋሩ ይገባል ብለዋል።

እድሳት የተደረገለት የኤምባሲው የቀድሞ ጽ/ቤት ህንጻ ከ1952 እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ እንደ ኤምባሲ ጽ/ቤት እና የሚሲዮን መሪ መኖሪያ ቤትነት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፥ ሚሲዮኑ አዲስ ወዳስገነባው ህንጻ መዛወሩን ተከትሎ ለረዥም ዓመታት ያለምንም አገልግሎትና እድሳት የቆየ መሆኑ በመርሐ ግብሩ ላይ ተጠቅሷል።

በ2013 ዓ.ም ሚሲዮኑ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጋር የህንጻ እድሳት ውል ስምምነት በመፈራረም እድሳቱ እንዲጀመር ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን ፥ የህንጻው እድሳት ስራ ሂደት መጠናቀቅ በሚሲዮኑ በኩል ለአገልግሎት ቀርቦ ሊያበረክት ከሚችለው ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር የሃገራችንን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል፡፡

በጂቡቲ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ በበኩላቸው ፥ በህንጻው እድሳት ወቅት በቅንጅት ለተንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ባለድርሻ አካላትን ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.