Fana: At a Speed of Life!

በማጃንግ ዞን በረዶ ቀላቅሎ የጣለ ዝናብ ከ3 ሺህ 800 ሄክታር በላይ ሰብል ላይ ጉዳት አደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ጎደሬ ወረዳ ሰሞኑን በረዶ እና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ዝናብ ምክንያት ከ3 ሺህ 800 ሄክታር በላይ ሰብል ጉዳት መድረሱን ተገለጸ፡፡
የጎደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ይስሀቅ አብርሀም በረዶ እና ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በወረዳው በሚገኙ በተወሰኑ ቀበሌዎች ከ3 ሺህ 800 ሄክታር በላይ የሰብል እርሻ፣ በአትክልት ፍራፍሬ እና በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡
በጉዳቱ ምክንያት ህብረተሰቡ የምግብ ዋስትናውን ለማግኘት ስለሚቸገር ከወዲሁ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካለት ጋር እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ አደጋ መከላከል ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋትቤል ሙን የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው÷ ከፌዴራል እና ከክልሉ መንግስት ጋር በመመካከር የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት እንሰራለን ብለዋል፡፡ የሚመለከታቸው አጋር አካላትም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ከክልል ግብርና ቢሮ ጋር ሁኔታዎችን በማመቻቸትም ወቅቱን ያማከለ የሰብል ዘር በመፈለግ አርሶ አደሩ ማሳውን ዳግም በዘር እንዲሸፍን ይደረጋል ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.