Fana: At a Speed of Life!

የምርምር ተቋማት በውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ በመስራት የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር አለባቸው- የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የምርምር ተቋማት በውሃ ዲፕሎማሲና ተግባቦት ላይ በትኩረት በመስራት ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ ገለጹ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲ እና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መማክርት ፎረም እያካሄደ ነው።

በፎረሙ ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋን ጨምሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች፣ የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ባለሙያዎች፣ የተቋማት የስራ ኃላፊዎች፣ በውጭ የሚኖሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።

ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጹህፎች በፎረሙ እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን÷ ፎረሙ በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት ከተፈጥሮ ጸጋዎቿ እንዳትጠቀም ጫና ሲደረግባት መቆየቱን የጠቀሱት ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ÷ ይህም በልማት ላይ ተጽእኖ አሳድሮ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ጫናውን በመቀልበስ ኢትዮጵያውያን በተለይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያኮራ ተግባር አከናውነዋልም ነው ያሉት።

ለግድቡ ስኬት ርብርብ እያደረጉ ለሚገኙ አካላት ምስጋና አቅርበው÷ በቀጣይም በኢትዮጵያና ህዝቦቿ ላይ ጫና የሚያሳድሩ አካላትን ጥረት የማክሸፍ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ዜጎች በራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገራቸው ጥቅም መከበር እያደረጉ ባለው ትግል ከፍተኛ ድል እየተመዘገበበት እንደሚገኝም ገለጸዋል።

የፎረሙ ዋና ዓላማም “ምን ብናደርግ የኢትዮጵያን ጥቅም እናስከብራለን” በሚለው ጉዳይ ላይ ምክክር ለማድረግ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም የምርምር ተቋማት በዲፕሎማሲ፣ በውሃ ልማትና ሚዲያ ዘርፉ ላይ በትኩረት በመስራት ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ውሃ ለኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መገለጫ ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት ፍላጎቷን ለማረጋገጥ በቀጠናው ለሚገኙ እንደ ጅቡቲና ሱዳን ላሉ አገራት ያላትን በማካፈል እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ከሌሎቹ የጎረቤት አገራት ጋር በትብብርና በጋራ ለመስራት ኢትዮጵያ በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህን አብሮ የመልማት ፍላጎት ለማስቀጠልም ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ የአገራቸውን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ የኢትዮጵያን እውነትም በተለያዩ ቋንቋዎች በማስረዳት የጀመሩትን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.