Fana: At a Speed of Life!

የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ትናንት የመጨረሻ የኮቪድ-19 ታካሚን ወደ ቤት ሸኝቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ኮቪድ ታካሚ አድሯል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለሁለት አመታት ኮቪድ19 የተገኘባቸውን ህመምተኞች ተቀብሎ ሲያክም የቆየው የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ትናንት የመጨረሻ ታካሚን ወደ ቤት ሸኝቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ኮቪድ 19 ታካሚ አድሯል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተገኘ በኋላ ሆስፒታሉ ላለፉት ሁለት አመታት ቀዳሚው የኮቪድ-19 ህክምና መዕከል ሆኖ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል።

በትናንትናው ዕለትም የመጨረሻውን ታካሚ ወደ ቤቱ በሰላም መሸኘቱን ሆስፒታሉ ያስታወቀ ሲሆን ÷በሁለት አመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆስፒታሉ ያለ ኮቪድ19 ታካሚ ውሎ ማደሩን ነው የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ያሬድ አግደው በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያመለከቱት።

ከዚህ በኋላ ሀገርን በሚጎዳ መልኩ የኮቪድ-19 ማዕበል በኢትዮጵያ በድጋሚ እንዳይከሰት ሁላችንም የድርሻችን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ ዶክተር ያሬድ አሳስበዋል።

በትላንትናው እለት በሃገር ደረጃ ለ3 ሺህ 579 ሰዎች ኮቪድ19 የላቦራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን÷ ከዚህ ውስጥ 39 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡

በእለቱም በቫይረሱ ለህልፈት የተዳረገም ሰው አልነበረም።

እንደ ኢፌደሪ ጤና ሚኒስቴር መረጃ በኢትዮጵያ አሁን ላይ 7 ሺህ 454 ሰዎች ቫይረሱ ይገኝባቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.