የሀገር ውስጥ ዜና

ሶማሊያ በመጪው ሰኔ 15 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንደምታካሂድ አስታወቀች

By Meseret Awoke

May 06, 2022

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 28፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ የተራዘመውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰኔ 15 እንደምታደርግ አስታውቃለች፡፡

የሶማሊያ ፓርላማ በዛሬው ዕለት እንዳስታወቀው፥ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በሰኔ አጋማሽ የሚካሄድ ሲሆን፣ ከሁለቱም ምክር ቤቶች 329 የህግ አውጭዎች፣ 54 የሰኔት አባላት እና 275 የታችኛው ምክር ቤት አባላት 10ኛውን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ሶማሊያ ከቅኝ ግዛት እንድትላቀቅ የነፃነት ትግሉን በግንባር ቀደምትነት ሲመራ የነበረው የሶማሊያ ወጣቶች ሊግ 79ኛ ዓመት በሚከበርበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ ምርጫውን ለሶማሊያውያን ልዩ ትርጉም አለው ተብሏል፡፡

የሶማሊ ምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ፕሬዚዳንታዊ እጩዎቹ ምርጫ ከመደረጉ በፊት ግንቦት 11 እና 12 በፖሊሲዎቻቸው ላይ ክርክር እንደሚያደርጉ አመላክቷል።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ከተያዘለት መርሐ ግብር 15 ወራት የዘገየ ሲሆን፥ ሶማሊያ በሚያዝያ ወር የፓርላማ አባላት ምርጫ ካጠናቀቀች በኋላ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀነ ቀጠሮ መያዟ ይታወሳል፡፡

በአውሮፓውያኑ የካቲት 8 ቀን 2021 የስልጣን ዘመናቸው በይፋ ያበቃው የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሞሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የሶማሊያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቀን ማለፉን ተከትሎ ጫና ውስጥ እንደነበሩ አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡