የሸዋል -ኢድ በዓልን አስመልክቶ ሐረርን ፅዱና ውብ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው- የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሚከበረውን የሸዋል -ኢድ በዓል አስመልክቶ ከተማዋን ፅዱና ውብ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ፡፡
በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት የከተማ ደረቅ ቁሻሻ አስወጋጅና የአረንጓዴ አካባቢ ልማት ሥራ አስኪያጅ ኢብራሂም አሕመድ÷ ዘንድሮ በድምቀት የሚከበረውን የሸዋል -ኢድ በአልን አስመልክቶ ከተማዋን ውብና ፅዱ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የሚገኙ የአስፋልት ዳርቻዎችን፣ አደባባዮችንና ታሪካዊ ቦታዎችን የማስዋብና የማደስ ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የሐረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
ከተማዋን ውብና ፅዱ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው÷ ማህበረሰቡ በአካባቢው የሚከናወኑ መሰረተ ልማቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡