Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 29 ነጥብ 83 ሚሊየን መድረሱን ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትየጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 29 ነጥብ 83 ሚሊየን መድረሱን እና የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ሰሞኑን የተካሄደ አንድ ጥናት አመለከተ።
የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር 119 ነጥብ 3 ሚሊየን አድርጎ የተሠራው ጥናቱ÷ በኢትየጵያ 29 ነጥብ 83 ሚሊየን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸውን አመላክቷል፡፡ ይህ ቁጥር ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 25 በመቶው መሆኑንና በኢትዮጵያ የሞባይልና በይነመረብ ተጠቃሚዎች እንዲሁም የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱም ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2021 በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2022 በ731 ሺህ ወይም በ2 ነጥብ 5 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡ ይህም የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ጭማሪ ቢያሳይም አሁንም 89 ነጥብ 5 ሚሊየን ሕዝብ ወይም 75 ከመቶው ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጭ ናቸውም ተብሏል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አሳሪ የሆኑ አሰራሮችን እየነቀሰ በማውጣት ምቹና ሊያሰራ የሚችል የሕግ ማዕቀፎችን እያዘጋጀ ሲሆን÷ ይህን የሕግ ማዕቀፍ አስፈፃሚ ተቋማት ወስደው ተፈፃሚ እንዲያደርጉም ተመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 መከሰትን ተከትሎ በይነመረብን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በ2022 የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነትን በተመለከተ÷ ኢትዮጵያ ውስጥ የሞባይል የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት 14 ሜጋ ባይት በሰከንድ፣ መካከለኛው ደግሞ 3 ነጥብ 31 ሜጋ ባይት በሰከንድ ነው ተብሏል፡፡ ይህ አሃዝ በ2022 መጨረሻ በኢትዮጵያ ያለው አማካይ የሞባይል የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት በ2 ነጥብ 8 ሜጋ ባይት በሰከንድ ጭማሪ ማሳየቱንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይህም በ12 ወራት ውስጥ በ17 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል ነው የተባለው፡፡
ቋሚ የበይነ መረብ ግንኙነት ፍጥነት በ0 ነጥብ 58 ሜጋ ባይት በሰከንድ ወይም 21 ነጥብ 2 ከመቶ መጨመሩም ተገልጿል፡፡
በ2022 ያለውን የሞባይል ግንኙነትን በተመለከተም÷ ከጂ ኤስ ኤም ኤ ኢንተለጀንስ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በ2022 መጀመሪያ ላይ 58 ነጥብ 54 ሚሊየን የሞባይል ተጠቃሚዎች መኖራቸው ተገልጿል፡፡ ይህ አሃዝ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 49 ነጥብ 1 በመቶ ነውም ተብሏል፡፡
ከ2021 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ያለው የሞባይል የበይነ መረብ ግንኙነት በ9 ነጥብ 4 ሚሊየን ወይም 19 ነጥብ 2 በመቶ መጨመሩን ጥናቱ አመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.