Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሃፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር ዋና ጸሃፊ አብደራህማን በርቴ ጋር ውጤታማ ውይይት ማካሄዳቸው ተገለጸ፡፡

ውይይትን ተከትሎም ዋና ጸሃፊ አብደራህማን በርቴ፥ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸው አንስተዋል።

አቶ መስፍን ጣሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሪነት ቦታ በተረከቡበት ወቅት የዋና ስራ አስፈፃሚዎች የአመራር ውይይት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንዲያደርጉ ስለተሰጠው እድል ማህበሩ ያመሰግናል ብለዋል ዋና ጸሃፊው።

“በዚህ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የማህበሩ ትብብር እንዲሁም የአፍሪካ አቪዬሽን እያደገ እንዲቀጥል እና በዓለም ላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሚና እንዲጫወት በሚያስችሉ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ላይ ውጤታማ ምክክር አድርገናል” ሲሉም ነው ያብራሩት፡፡

ዋና ጸሃፊው አክለውም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1968 የማህበሩ መሥራች ከሆኑት 15 አባላት መካከል አንዱ መሆኑን አውስተው ፥ የአየር መንገዱና የማህበሩ ቀጣይነት ያለው ትብብር ለማህበሩ ራዕይ መሳካት አስፈላጊ ነውም ብለዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ እና ሌሎች ከፍተኛ የአመራሮች ተገኝተዋል።

ማህበሩ 44 የአፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን ፥ የማህበሩ አባላት በአፍሪካ አየር መንገዶች ከሚጓዙት አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የአየር ትራፊክ እንቅስቃሴን ከ85 በመቶ በላይ እንደሚሸፍኑ ሎጂስቲክስ አፕዴት አፍሪካ ዘግቧል።

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.