በደቡብ ክልል በሦስት ዓመታት 40 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እስከ 40 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተመለከተ ።
የደቡብ ክልል የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት መንደር ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ ቦኖሾ ጎልቾ ቀበሌ ተካሂዷል።
በፕሮጀክቱ አንድ አርሶ አደር በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 100 የፍራፍሬ ችግኝ የሚተክል ሲሆን ፥ 30 በመቶው በመጀመሪያው ቀሪውን 40 እና 30 በመቶ ደግሞ በ2ኛና በ3ኛ ዓመት የሚተክልበት መርሐ ግብር መሆኑ ተመላክቷል።
መርሐ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ከላሰተር አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ናቸው።
አቶ ኡስማን ፥ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ በልማት ስራ በማሳተፍ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በተመረጡ የአቮካዶ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና አፕል ተክሎችን ላይ መሠረት ያደረገ የፍራፍሬ መንደር መመስረትን ያለመ መሆኑንም አክለዋል።
“ልማቱን ማሳካት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው” ያሉት አቶ ኡስማን ፥ በተለይ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ ስራ አጥነት እንዲቀንስና ከቤተሰብ እስከ ሀገር ብልጽግናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ክልሉን የማልማት አቅምን መሠረት ያደረገው የፍራፍሬ መንደሮች ምስረታ፥ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የልማቱ ተሳታፊዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
አንድ አርሶ አደር በሶስት አመት ጊዜ ውሰጥ 100 የተዳቀሉና ምርታማ የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክል እንደሚደረግ ጠቅሰው ፥ የመንግስትና የህብረተሰብ ተቋማት ደግሞ ከ100 እስከ 10 ሺህ የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክሉ እቅድ መያዙን አስረድተዋል።
በፕሮጀክቱ ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማስተባበርና የመንግስትን ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ህብረተሰቡን ከድህነት ማውጣት ይቻላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ክፍት መሬት ባላቸው ተቋማት ውስጥ ሁሉ የሚተገበር መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው ፥ በክልሉ ተመሳሳይ ስነ-ምህዳርን መሠረት በማድረግ 26 የፍራፍሬ መንደርን ለመመስረት ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በጥናቱ መሰረት በዚህ ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኝ ለመትከል መታቀዱ ነው የተጠቆመው፡፡
በሶስት ዓመት ውስጥም ከ30 እስከ 40 ሚሊየን የፍራፍሬ ችግኝ በማሰራጨትና በማልማት በክልሉ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ልማቱን በትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማትም ተግባራዊ ለማድረግ በተማሪዎችና በምእመኑ የችግኝ አቅርቦትና ተከላ እንደሚፈጸም አስረድተዋል።
በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው፥ ማህበራዊ ተቋማት ተልእኳቸውን ከመወጣት ማሻገር በድህነት ቅነሳ ላይ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።