Fana: At a Speed of Life!

ለመኽር ወቅት እርሻ ጅቡቲ ወደብ ከደረሰው 7 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 75 በመቶው ወደ ማዕከላዊ መጋዘን ገብቷል -የግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ለ2014/15 የመኽር ምርት ዘመን ጅቡቲ ወደብ ከደረሰው 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 75 በመቶው ወደ ማዕከላዊ መጋዘን መግባቱን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ÷ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ነው ያሉት።

በተለይ ክረምቱ ከገባ በኋላ ተሽከርካሪ ማስገባት ለማይቻልባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የማዳበሪያ ግብዓቱን የማድረስ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።

በእነዚህ አከባቢዎች እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ ግብዓቱን በሙሉ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው፥ ሌሎች ቦታዎችም በቅደም ተከተል የማሰራጨት ስራው እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡

የማዳበሪያ ስርጭቱ ፍትሃዊ ይሆን ዘንድም አሰራሮች መዘርጋታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ ማዳበሪያን በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር እና ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዲኖር የሚያደርጉ አካላት ላይ ልዩ ክትትል እየተደረገ መሆኑንና በህገ ወጦች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስጠነቀቁት።

ለመኽር ወቅት የምርጥ ዘር አቅርቦትን በሚመለከትም ከሚያስፈልገው ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነውን ማሟላት ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ፥ በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ሁለተኛ ደረጃ ምርጥ ዘርን መጠቀም በአማራጭነት መያዙን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይም የ2014/15 የመኽር ወቅት ውጤታማ እንዲሆን ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ተናግረዋል፡፡

 

በዙፋን ካሳሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.