Fana: At a Speed of Life!

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ከቻይና መንግስት ኮንስትራክሽን እና ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28፣ 2014 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ ከቻይና መንግስት ኮንስትራክሽን እና ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ዙሪያ ተወያዩ።

በውይይቱ አቶ ቀጄላ በካምፓኒዉ የቀረበ የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄን በተመለከተ የዶላር ቅድመ ክፍያ ሳይከፈል በመቆየቱ፣ የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ ከዜ ወደ ጊዜ እየናረ መሄዱን ተከትለዉ የብሔራዊ ስቴድየሙ ግንባታ ሂደት ላይ መጓተት በመፍጠሩ አጠቃላይ የአለም የዋጋ ማስተካከያ መርሆን መሰረት ያደረገ ዋጋ ማስተካከያ እንደሚደረግ ለተቋራጭ ካምፓኒዉ አረጋግጠዋል።

የውጭ ምንዛሪ ክፍያን በተመለከተ መንግስት ለፕሮጀክቱ ትኩረት በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ቅድመ ክፍያ ጥያቄን ለመመለስ ገንዘቡ ከባንክ እንዲለቀቅላቸው ቢያመቻችም ካምፓኒዉ የዋጋ ማስተካከያ ይደረግልኝ ጥያቄዬ መልስ ካለገኘ በሚል ክፍያው ሳይፈጸም የቆየ መሆኑ ተገልጾ ውይይት ከተደረገ በኋላ ካምፓኒው ገንዘቡን ተረክቦ ቀሪውን ግንባታ እንደሚያከናውን ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

ከውጭ ለሚገዙ እቃዎች ቀብድና ሙሉ ክፍያ ለመፈፀም፣ ለትራንስፖርትና ለወደብ ክፍያ የሚፈለገው መስተጓጎል እንዳይኖር የውጭ ምንዛሪ ክፍያው ተጀምሮ እንዳይቋረጥ በኮንትራክተሩ የቀረበውን ጥያቄ በመንግሥት በኩል ፕሮጄክቱን ለማጠናቀቅ ሲባል በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተገልጿል።

ቀጣይ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም እና ሙያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የቴክኒክ ውይይቶች በየጊዜው እየተደረጉ እና የውሳኔ ሀሳቦች ለአመራሩ እንድቀርቡ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን ÷ አማካሪው እና የፕሮጀክቱ ተቋራጭ በቅንጅት በመሥራት ስራውን በስኬት ማጠናቀቅ እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.