Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቡናን በቻይና ገበያ በስፋት ለማቅረብ የሚያግዝ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ቡና በቻይና ገበያ በስፋት እንዲሸጥ ለማድረግ ያለመ ለቻይና ቡና ነጋዴዎች በበይነ መረብ የማስተዋወቅ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡
በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ “ቡናን ከምድረ ቀደምት” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮጵያን ቡና ለቻይና ቡና ነጋዴዎች የማስተዋወቅ መርሐ ግብር ከ50 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ነው የተካሄደው፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ ኤዥያ እና ፓስፊክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ገበየሁ ጋንጋ÷ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል የንግድ ትስስር እያደገ መምጣቱን ገልጸው÷ የአገራችን ቀዳሚ የወጪ ምርት የሆነው ቡና ወደ ቻይና ገበያ በስፋት መላክ ይቻል ዘንድ የዘርፉ ላኪዎችን እና ተረካቢዎችን በማገናኘት መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ÷ የሁለቱ አገሮች የረጅም ጊዜ ወዳጅነት በበርካታ ዘርፎች እየተጠናከረ መሄዱን ጠቁመው÷ የኢትዮጵያ ቡና በኤሌክትሮኒክ ግብይት አማራጭም ጭምር ወደ ቻይና ለመላክ እንዲቻል የውይይት መድረኩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
በቻይና የቡና ማህበራት ተወካይ በቻይና ከትላልቅ ከተሞች እስከ መለስተኛ ከተሞች የቡና ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ማሳየቱን ገልጸው÷ ለኢትዮጵያ ቡና አምራቾች እና ላኪዎች ሰፊ የገበያ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና የሚላክ ቡና መጠኑ እየጨመረ መሄዱንም አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወገንም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ተወካዮች በኢትዮጵያ ያለውን የቡና ምርታማነትና ጥራት ያለውን ከፍተኛ ማብራራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.