Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው የተጓተተው አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት መስተጓጎል ፈጥሮበታል የተባለው አዲሱ የአባይ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።
የድልድዩ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ተጠሪ ኢንጂነር ፍቅረስላሴ ወርቁ ድልድዩ÷ በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የአባይ ድልድይ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ድልድዩ በአንድ ጊዜ ስድስት ተሽከርካሪዎችን ማስተላለፍ የሚችል ባለሁለት አካፋይ ያለውና አምስት ሜትር የሳይክልና የእግረኞች መንገድ ማካተቱን እንዲሁም የትራፊክ ምልክቶች፣ የድልድይ ላይ መብራቶች፣ የተሽከርካሪ መውጫና ሌሎች የኮንክሪት መዋቅሮች መያዙንም ተናግረዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም የተጀመረው ፕሮጀክት በ2013 ዓ.ም መጨረሻ መጠናቀቅ የነበረበት ቢሆንም÷ እስካሁን ያለው የግንባታ አፈጻጸም 61 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጦርነት ምክንያት በግንባታ ግብአት አቅርቦት ላይ ጫና በመፍጠሩ ፕሮጀክቱን በተባለው ጊዜ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
የግብአት አቅርቦት በሚፈለገው መጠን ከተሟላ ፕሮጀክቱን በ2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ እቅድ መያዙንና ለዚህም አስፈላጊው ድጋፍ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.