ሰሜን ኮሪያ በሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 29፣2014 (ኤፍ ቢሲ) ሰሜን ኮሪያ በጃፓን ባህር ሚሳኤል ማስወንጨፏን የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አዛዦች አስታወቁ።
ሰሜን ኮሪያ ያደረገችው የሚሳኤል ሙከራ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን በተያዘው የፈረንጆቹ አመት ውስጥ ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ የተሞከረ መሆኑን የደቡብ ኮሪያው ዮንሃፕ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ወር መጨረሻ በሰሜን ኮሪያ በተደረገው ወታደራዊ ትርኢት የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማበልጸግን እንደሚያስቀጥሉ እና አስፈላጊ ከሆነም ሀገራቸውን ለመከላከል ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት መግለጻቸው ይታወሳል።
አሁን የተሞከረው የሚሳኤል አይነት ባይገለጽም ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሳይሆን እንደማይቀር ነው የተገለጸው።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የሚሳኤል ሙከራ ለማድረግ ተዘጋጅታለች ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ፒዮንግያንግ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባትሰጥም የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ራስን ለመከላከል እንደምትፈልግ መግለጿን አር ቲ በዘገባው አስታውሷል።