Fana: At a Speed of Life!

በታንዛኒያ በእስር ላይ የሚገኙ 4 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን በምሕረት እንዲለቀቁ ስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 29 ፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በታንዛኒያ በሕገ-ወጥ መልኩ በመግባት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ 4 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን በምሕረት እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ መደረሱን በዳሬሰላም የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

ስምምነቱ የተደረሰው በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ቀዲዳ በዛሬው ዕለት በታንዛኒያ የኢሚግሬሽን ኮሚሽን በመገኘት ከኢሚግሬሽን ኮሚሽነሩ ዶክተር አና ፒ ማካካላ እና የታንዛኒያ የድንበር ቁጥጥር እና አስተዳደር ኮሚሽነር ሳሙኤል ማሂራኔ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው።

አምባሳደር ሽብሩ በውይይቱ ወቅት ለተደረገላቸው አቀባበል ኮሚሽነሮቹን አመስግነው በታንዛኒያ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱን አገራት ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ከማሳደግ አንጻርም የታንዛኒያ መንግሥት በሕገ-ወጥ መልኩ ወደ ታንዛኒያ በመግባት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ ላሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ምሕረት እንዲያደርግ እና ከእስር እንዲፈታ ጥያቄ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሮቹ በበኩላቸው አምባሳደሩ ያነሱትን የምሕረት ጥያቄ በተመለከተ በአጠቃላይ በታንዛኒያ በእስር ላይ ለሚገኙት 4 ሺህ 500 የሚሆኑ ዜጎች የታንዛኒያ መንግሥት በሙሉ ምሕረት የሚያደርግ መሆኑን እና ሁሉም ከእስር ተፈትተው ወደ አገራቸው እንዲገቡ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል።

በቀጣይ የምሕረት ሂደቱ የአገሪቱን ሕግ በተከተለ መልኩ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ የሚፀድቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕጋዊ ሂደቶቹ እስከሚጠናቀቁ ድረስ ፍርዳቸውን ያጠናቀቁት ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ሂደት እንዲጀመር ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የሥራ ክፍሎች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.