Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች በልማት ስራ ሊሰማሩ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 29 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ታጣቂዎች በልማት ስራ ሊሰማሩ ነው።

ሰላምን አማራጭ አድርገው ወደ ህብረተሰቡ ለሚቀላቀሉ ታጣቂዎች በመተከል ግልገል በለስ የተሀድሶ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።

በተሃድሶ ስልጠና ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ታጣቂዎቹ የሠላምን አማራጭ ተቀብለው መምጣታቸው ታሪካዊ ውሳኔ ነው ብለዋል።

ከዳንጉርና ማንዱራ ወረዳዎች የተውጣጡት እና ለዓመታት በጫካ ውስጥ የነበሩት ከአንድ ሺህ በላይ ታጣቂዎች ከእነትጥቃቸው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መመለሳቸው ለሰላም ምን ያህል ቁርጠኛ መሆናቸውን በተግባር ያሳያል ተብሏል።

ክልሉ ታጣቂዎቹን በተለያየ የስራ መስክ ላይ እንዲሰማሩ ዝግጅት ማድረጉንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ሌ/ጀኔራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው፥ ታጣቂዎቹ በሰላም አብሮ ለመኖር በተደረገው ጥሪ መሠረት በገዛ ፈቃዳቸው ትጥቅ ፈተው የልማት አምባሳደር ለመሆን በመምጣታቸው በኮማንድ ፖስቱ ስም ምስጋና አቅርብዋል።

ጀነራል መኩንኑ የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች ለሰላም ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀው ከእንግዲህ ጥይት የሚተፋ ሳይሆን ለልማት የሚውል መሳሪያን መሸከም አለባችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሁለት ዙር የተሰጠውን ስልጠና ያጠናቀቁት ታጣቂዎች በህገ-መንግስት፣ በወንጀል መከላከል፣ ስለወንጀል አስከፊነት እና የስራ ዕድል ፈጠራን አስመልክቶ በተለያዩ የዞኑ አመራሮች ስልጠና መውሰዳቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል።

የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች 155 ክላሽንኮቭ፣ 97 የተለያዩ ኋላቀር መሳሪያዎች ፣ 82 የተለያዩ የእጅ ቦንቦች ፣ 2 ብሬን ፣ ከ2 ሺህ በላይ ቀስት፣ ከ3 ሺህ በላይ የተለያየ መጠን ያላቸው ስለታማ ነገሮች እንዲሁም ከ1 ሺህ በላይ የክላሽንኮቭ እና የኋላ ቀር መሳሪያ ጥይቶችን አስረክበዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.