Fana: At a Speed of Life!

በነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ላለፉት አራት ወራት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ የምርቶቹ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ ተደረገ።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ ከነገ ሚያዚያ 30 ጀምሮ በነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ማድረጉን አስታውቋል።

በታህሳስ ወር ቤንዚን በሜትሪክ ቶን 870 የአሜሪካን ዶላር እና ናፍጣ በሜትሪክ ቶን 730 የአሜሪካን ዶላር ይሸጥ ከነበረበት ሚያዚያ ወር ላይ ቤንዚን በሜትሪክ ቶን ወደ 1028 የአሜሪካ ዶላር እና ናፍጣ ደግሞ በሜትሪክ ቶን ወደ 1138 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ማለቱን አንስቷል ሚኒስቴሩ በመግለጫው።

መንግስት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ ከታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ወራት ምንም አይነት ጭማሪ ሳያደርግ ቤኒዝኒን በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 28 ብር ከ98 ሳንቲም እንዲሸጥ ወስኖ ቆይቷልም ነው ያለው።

ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በወር በአማካይ ወደ ተጠቃሚው መተላለፍ የነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዲመዘገብና በመንግስት ላይም ከፍተኛ ጫና ማስከተሉን አስረድቷል።

በሚያዚያ ወር በዓለም ገበያ ነዳጅ የተገዛበት መሸጫ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ ቀጥታ ተሰልቶ ተግባር ላይ ቢውል በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ሊትር ናፍጣ መሸጫው 73 ብር እንደዚሁም የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ዋጋ 66 ብር ከ78 ሳንቲም ይሆን ነበርም ብሏል።

ሆኖም ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከዓለም መሸጫ ዋጋ ልዩነትን 85 በመቶ የሚሆነውን ጫና መንግስት በመሸከም ቀሪውን 15 በመቶ ለተጠቃሚው እንዲተላለፍ በመወሰን የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ ማድረጉን ነው ያስታወቀው።

በዚህም መሰረት ከነገ ሚያዚያ 30 ጀምሮ በአዲስ አበባ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ቤንዚን በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 52 ብር ከ45 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 51 ብር ከ78 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 78 ብር ከ87 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል።

ነገር ግን ይህንን መጠነኛ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ክለሳን ምክንያት በማድረግ በእቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩና በምርቶች ላይ ዋጋን የሚያንሩ ህገወጥ አካላት ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፥ በየደረጃው ከሚገኘው የመንግስት መዋቅር ጋር በመሆን የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.