የአምስቱ አጎራባች ክልሎች ኢግዚቢሽንና የባህል ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ተከፈተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የአምስቱ አጎራባች ክልሎች ኢግዚቢሽንና የባህል ፌስቲቫል በሀረር ከተማ ተከፈተ።
የ”ከኢድ እስከ ኢድ” ሃገራዊ ጥሪ አካል የሆነውና በሐረሪ ብሔረሰብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል አንዱ አካል የሆነው የአምስቱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ኢግዚቢሽንና የባህል ፌስቲቫል በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እና በሐሪሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አርዲን በድሪ ተከፍቷል።
በኢግዚቢሽንና ባህል ፌስቲቫሉ ላይ የሐረሪ፣ የሶማሌ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልሎችና የድሬዳዋ ከተማ አሰተዳደር ተወካዮች የተለያዩ ባህላዊ የእዳ ጥበብ ውጤቶችና የቤት ዉስጥ መገልገያዎችን እንዲሁም ባህላዊ አልባሳትና ጭፈራዎችን እያሳዩ ይገኛሉ።
የሸዋል ኢድ በሐረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ከኢድ አልፈጥር በዓል በኋላ ለስድስት ቀናት ተጹሞ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶችን ባስተሳሰረ መልኩ በጋራ የሚከበር ሲሆን፥ የዘንድሮው ሸዋል ኢድ ለየት ባለ መልኩ ኢድን በማክበር ከመጡ ዲያስፖራዎች ጋር እየተከበረ ይገኛል፡፡
በተሾመ ኃይሉ