ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማለፉን አደነቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ቡድን በኒጀር ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ማለፉን አደነቁ፡፡
ከንቲባ አዳነች ኢትዮጵያን ወክሎ በኒጀር የአፍሪካ ዋንጫ ለሚሳተፈው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ እጅ ኳስ ቡድን በኢትዮጵያ ሆቴል ተገኝተው ሸኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ “እናንተ በመሳተፋችሁ ከውጤትም በላይ ባንዲራችን ከፍ ብሎ ይውለበለባል፤ ሀገራችንን በማስተዋወቅ ትልቁን አሻራችሁን በማስቀመጣችሁ ልትመሰገኑ ይገባል” ብለዋል፡፡
በአንድ ክፍለ ከተማ ቡድን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ ማየት እንደሚያስደስታቸው ገልጸው÷ ቡድኑ በድል እንዲመለስም እዚህ ያሳየውን ብቃት ሊደግመው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚና የቡድኑ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ÷ ቡድኑ የተጣለበትን ሀገራዊ አደራ በብቃት በመወጣት በውጤት እንደሚመለስ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ እንደሚያመላክተው÷ቡድኑ ከዚህ በፊት ካይሮ ላይ በተካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ በስኬት ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡