Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው በተደራጀ አግባብ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቅ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት በተደራጀ አግባብ በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ጥሪ አቀረበ፡፡
“የአገረ መንግስት ግንባታና የዳያስፖራ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ “ከኢድ እስከ ኢድ ወደ አገር ቤት “ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ከመጡ ዳያስፖራዎች ጋር በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የነበረው ውይይት ተጠናቋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሃሺ ባደረጉት ንግግር÷ “የዳያስፖራ አባላት ብሄርና ሃይማኖት ሳይገድባችሁ በተደራጀ አግባብ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ መትጋት ይጠበቅባችኋል” ብለዋል፡፡
የዳያስፖራ አባላት በሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሳተፍ፣ ለሰላምና ለማህበራዊ ዕድገት ያላቸውን ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀው÷ ለዚህም የክልሉ መንግስት ዳያስፖራው የሚያከናውናቸውን የልማት ተግባራት ለመደገፍና አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እድሪስ ÷የዳያስፖራ አባላት በሚኖሩበት ሀገር ያገኙትን ልምድና እውቀት በመጠቀም በኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ሀገረ መንግስት መተግበር እንዲቻል አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
በኢንቨስትመንት፣ በእውቅትና ክህሎት ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሬ በመላክ እያበረከተ ያለው አስተዋጾ ጠንካራ እንዲሆን የውይይት መድረኮች ወሳኝ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው ወደ ሚኖሩበት ሀገር ሲመለሱ÷ ኢትዮጵያን በተሻለ ሁኔታ ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ግብዓት ከመድረኩ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.