Fana: At a Speed of Life!

የሩስያ ሰራዊት በደቡብና ምስራቃዊ ዩክሬን ጥቃቱን እያጠናከረ መሆኑ ተነገረ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩስያ ሰራዊት ሁለተኛዋን የዩክሬን ትልቅ ከተማ ማሪዮፖልን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በማሰብ በደቡብና ምስራቃዊ የዩክሬን ግዛቶች ጥቃቱን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ተነገረ።

የሩስያ ጦር ትናንት በሉሃንስክ ክልል የቦንብ ጥቃት መፈጸሙንና በአንድ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የ60 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል።

ሩስያ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበት ብሄራዊ የድል በዓል መታሰቢያ ነገ ሰኞ ሲከበር÷ የሩስያ ሰራዊት ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ሊከፍት ይችላል የሚል ስጋት መኖሩንም የዓለም መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት “የአንድነት ኃይል” የተባለው የጋራ ጦር÷ የአውሮፓ ከተሞችን ከናዚ ጦር ነፃ ያወጣበትን የድል ቀን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በስሜት ተሞልተው ባደረጉት ንግግር፥ “ ሰይጣን መልኩን፤ ቅርጹንና መፈክሩን ቀይሮ እንደገና ወደ ዩክሬን መጥቷል፤ ነገር ግን እናሸንፈዋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዛሬ 74ኛ ቀኑን በያዘው በሩስያ- ዩክሬን ጦርነት፥ የሩስያ ጦር ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ እየተጠጋ መሆኑም የቲ አር ቲ ዘገባ ጠቁሟል።

የሩስያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬን በምትገኘው በሉሃንስክ ክልል ትናንት በፈጸመው የቦንብ ጥቃት ቢልሆሪቭካ በተባለ ቀበሌ የሚገኝ ትምህርት ቤት የጥቃት ዒላማ በመሆኑ 60 ሰዎች በፍርስራሹ ተቀብረው ህይወታቸው ማለፉን የዩክሬን ባለስልጣናት ገልጽዋል።

ከቦምብ ጥቃት ለመትረፍ በማሰብ 90 የሚሆኑ ሰዎች በትምህር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰፍረው እንደነበርና ሌሎች 30 ሰዎች ከሞት መትረፋቸውንም ባለስልጣናቱ ጨምረው ተናግረዋል።

ድርጊቱን አጥብቆ ያወገዘው የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፥ ሞስኮ “አረመኔያዊ ጥቃት” ማካሄዷንና በ2ኛው የዓለም ጦርነት የተፈጸመውን አሳዛኝ ድርጊት እየደገመች እንደሆነ ገልጿል።

ይህን የሩስያ ድርጊት ነገ ሰኞ ከሚከበረው ሶቭዬት ኀብረት በናዚ ጀርመን ላይ የተቀዳጀችው የድል በዓል ጋር በማያያዝም የፖለቲካ ተንታኞች ለየት ያለ ትርጉም ሰጥተውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሪታንያ ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አገራቸው የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ፖውንድ (1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር) ወታደራዊ ዕርዳታ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን ነው ያስታወቁት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ” ሩስያ እያጠቃች ያለችው ዩክሬንን ብቻ ሳይሆን የመላው አውሮፓን ሰላምና ደህንነት ጭምር ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ነው የገለጹት።

ይህ የብሪታንያ ድጋፍ ይፋ የተደረገውም ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰንን ጨምሮ የቡድን 7 አባል አገራት ማለትም የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓንና የአሜሪካ መሪዎች የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪን ዛሬ ለማነጋገር ቀጠሮ በያዙበት ወቅት መሆኑም ተመላክቷል።

የአሁኗ ሩስያ (የቀድሞዋ ሶቭዬት ኀብረት) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመንን ያሸነፈችበትን 77ኛ ዓመት የድል በዓል ነገ በአገር አቀፍ ደረጃ ስታከብር፥ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለመላው የሩስያ ሕዝብ በተለይም ለሩስያ ሰራዊት ለየት ያለ ንግግር እንደሚያደርጉና ልዩ ወታደሪያዊ ዘመቻ ሊከፍቱ ይችላሉ የሚል ስጋት መኖሩን በርካታ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በሌላ በኩል የአሜሪካዋ ቀዳማዊት እመቤት ጅል ባይደን በስሎቫኪያ የሚገኙ የዩክሬን ስደተኞችን ጎብኝተዋል።

ጅል ባይደን የዓለም የእናቶች ቀን እየተከበረ ባለበት በዛሬው ዕለት ስደተኞቹን በጎበኙበት ወቅት÷ የሩሲያና የዩክሬን ግጭት ” ትርጉም አልባ ” ነው ብለውታል። ጅል ባይደን ያነጋገሯቸው የዩክሬን ስደተኞችም ፥ “አገራችንን ለቀን ብንወጣም ወደ አገራችን ተመልሰን ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት አለን” ብለዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.