Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተለያዩ አካላት የዘንድሮውን የቤት እድሳት መርሐ ግብር እንዲደግፉ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የዝናብ ወቅት ከመግባቱ በፊት የቤት እድሳት መርሐ ግብርን እንዲደግፉ ለተለያዩ አካላት ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማለዳ አዋሬ አካባቢ የሚኖሩ የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ዓመታዊ መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብር መጀመሩን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ “በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገውን ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብርን ስንጀምር ግለሰቦች፣ የንግድ ተቋማትና የመንግሥት ተቋማት ክረምት ከመግባቱ በፊት በአካባቢያችን ላሉ በርካታ ሰዎች ምቹ እና ሰብአዊ ክብርን መሠረት ያደረገ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ዓመታዊ ክንውን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል፡፡
በተለይም የንግድ ድርጅቶች ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ኑሮ ማሻሻል ይችላሉ ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ዓመታዊ እንቅስቃሴ ያስጀመሩት ከአራት ዓመታት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነትን በተቀበሉበት የመጀመሪያ ዓመት ሲሆን÷ ዓላማውም የአረጋውያን፣ የአቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና በኢኮኖሚ የተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤት ለማደስ ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ በየዓመቱ ክረምት ከመግባቱ በፊት የቤት እድሳት መርሐ ግብር ሲከናወን ቆይቷል።
በዚህ ዓመት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ‘የመደመር መንገድ’ ከተሰኘው መጽሐፋቸው ሽያጭ በተገኘ ገንዘብ÷ በአዋሬ አካባቢ ተለይተው ለታወቁ 23 ግለሰቦች የመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚደረግበትን ሂደት ማስጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.