ከ34 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰልጣኞች የሚሳተፉበት የስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር 3ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና ለመስጠት የማስጀመርያ መርሐ ግብር አካሄደ፡፡
በስልጠናው በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በ20 ከተሞች በ35 የስልጠና ማዕከላት ከ34 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው ገልፀዋል።
ሶስተኛው ዙር ስልጠና ከመጀመሪያዎቹ የሚለየው በስልጠናው የሚሳተፉ ሰልጣኞች ቁጥር በ10 እጥፍ መጨመሩ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ÷ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሀገሪቱ ብቸኛ የፖሊሲ ባንክ እንደመሆኑ በመንግስት ቅድሚያ ትኩረት የተሰጣቸው የልማት ውጥኖች በፕሮጀክት እና በሊዝ በፋይናንስ በመደገፍ ለሀገራችን ልማትና እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ከሚያከናውናቸው በርካታ ስራዎች በተጨማሪ እውቀቱ፣ ክህሎቱ እና ፍላጎቱ ኖሯቸው የኢንቨስትመንት መነሻና የብድር ማስያዣ ሀብት ማግኘት ላልቻሉ ወጣቶች ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫና የክህሎት ማዳበሪያ ስልጠና እንደሚሰጥም ተገልጿል።
በቅድስት ተስፋዬ