የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ማዕከል ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት በትምህርት ደረጃ ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ ያደረገው የኢትዮጵያ አገር በቀል እውቀት ማዕከል ተመሰረተ፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው እንዳሉት ፥ ለመጪው ትውልድ ጠቃሚ ልምዶችን ለማስተላለፍ እንዲቻል የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት ማእከል መመስረቱ ተገቢ ውሳኔና የሚያበረታታ ተነሳሽነት ነው፡፡
ሚኒስትሯ አክለውም እንደ ቻይና፣ ታይላንድና ጃፓን የመሳሰሉት ሃገራት በሳይንስና ምርምር አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ መሰረታቸው ሀገር በቀል እውቀት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ እውቀትን ለትውልዱ በሚገባ በማስተማር ተጠቃሚ ማድረግ፣ የግብረግብ ትምህርትን በስፋት ማስተማር፣ ስለ እፅዋት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ስለ መድኃኒት እጽዋት፣ ስለ ጥንታዊ ስእሎች አሳሳል፣ ስለ ቀለማት አቀማመም እና ስለ ጂኦሎጂ የድንጋይ ጥበብ ማስተማር ሀገራችን የተያያዘችውን የብልጽግና ጎዳና የሰመረ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ማለታቸውን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ብዝሓ ኢንስቲቲዩት ሃላፊነትና ተግባር የቀረበ ሲሆን ፥ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦችና ተመራማሪዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ሰፋ ያለ ምክክርና ውይይት በማካሄድ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ አገር በቀል ዕውቀት ማበልጸጊያ ማዕከልን ሁሉም በሚችለውና አቅሙ በፈቀደው መጠን እንደሚያገለግል ቃል ተገብቷል፡፡