Fana: At a Speed of Life!

የዲጂታል ክህሎት ያለው ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት ሊቋቋሙ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ክህሎት ያለው ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት ሊቋቋሙ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷ ማዕከላቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ስልጠናዎችን ለማግኘትና የብቃት ማረጋገጫ ለመውሰድ የሚያገለግሉ እንዲሁም ስራ መፍጠር የሚችልና ተወዳዳሪ የዲጂታል ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
ማዕከላቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት ጋር በመተባበር እንደሚያቋቁማቸው እና ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የሳይንስ ካፌዎችን እና የወጣቶች ማዕከላትን በማካተት እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡
የአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት የአፍሪካ ክልል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አኒ ራቼል ኢነ አለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት በኢትየጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከላትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡
ማዕከላቱን ለማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአለም አቀፉ የቴሌኮም ህብረት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መካሄዱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ማዕከል እንዲሆኑ ከተመረጡ ስምንት የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗንም መረጃው አመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.