14ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመከላከያ፣ የጸጥታና ደኅንነት መደበኛ ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ሕብረት የመከላከያ፣ የጸጥታና ደኅንነት 14ኛ መደበኛ ጉባዔውን ማካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከዛሬ ግንቦት 1 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አፍሪካ ህብረት ዋና መሥሪያ ቤት የሚካሄድ ሲሆን፥ የህብረቱ አባል አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
በጉባኤው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ግጭቶችን ፣ ሽብርተኝነትንና ፅንፈኝነትን እንዲሁም እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለማስቆም እየተከናወነ ያለውን ጥረት ሪፖርት እንደሚያቀርብ ተነግሯል።
የሕብረቱን ተጠባባቂ ሃይል አቅም ለማሳደግም እየተደረገ ያለው ድጋፍና ስምሪት ላይ ያተኮረ ሪፖርት ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።
የህፃናትን ደህንደነት ለመጠበቅ የተዘጋጀውን ረቂቅ ፖሊሲ በአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ፖሊሲ ውስጥ ለማካተት ያለመ ውይይት እንደሚካሄድም ተመላክቷል፡፡