ፍርድ ቤት-መር የአስማሚነት ማዕከላትን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 24፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ፍርድ ቤት-መር የአስማሚነት ማዕከላትን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙ ተገለጸ፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የኢትዮጵያ የማስማማት እና የግልግል ዳኝነት ማዕከል በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ የተቋቋሙ ፍርድ ቤት-መር የማስማሚያ ማዕከላትን በጋራ ለማጠናከር የሚያስችላቸው የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱን በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተፈራረሙት የፍርድ ቤቱ ም/ፕሬዜዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ እና የኢትዮጵያ የማስማማት እና የግልግል ዳኝነት ማዕከል የቦርድ ሊቀመንበር ወ/ሮ ሀረገወይን አሸናፊ ናቸው፡፡
በሁለቱ አካላት የተደረሰው ስምምነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ የተቋቋሙት ፍርድ ቤት-መር የማስማማት ማዕከላት እንዲጠናከሩና ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ የማስማማት እና የግልግል ዳኝነት ማዕከል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያቋቁማቸው ፍርድ ቤት-መር የአስማሚነት ማዕከላት የሎጅስቲክስ ድጋፍ በማድረግና አስፈላጊ ግብአቶችን በማሟላት ለሥራ ምቹ እንደሚያደርግ ተገለጿል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ በስሩ ለሚገኙ ለሁሉም የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶችና ባለድርሻ አካላት በፍ/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የማስማማት አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት መቋቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡
በዚህም ሁሉም የፍ/ቤት ዳኞች የማስማማት ጉዳዮችን ወደማዕከሉ መላክ እንዳለባቸው በማስገንዘብ የማስማሚያ ማዕከላቱ ተገቢውን ግልጋሎት እየሰጡ መሆናቸውንም እንዲያረጋግጥ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ማዕከሉም በዚህ ዙሪያ ሥልጠና የሚሰጡ አሠልጣኞችን በማዘጋጀት ሥልጠና የሚሰጥበትን ሁኔታ የሚያመቻች ሲሆን ለእያንዳንዱ የሥልጠና መስክ ሁለቱ ወገኖች በጋራ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን በማውጣት እጩ ሰልጣኞችን በጋራ ይመለምላሉ ነው የተባለው፡፡
በተመሳሳይም ማዕከሉ ከፍርድ ቤት-መር አስማሚነት ጋር የተያያዙ ሕጎች በየጊዜው እንዲሻሻሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ያግዛል፡፡
ማዕከሉ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋር በመተባበር ፍርድ ቤት-መር አስማሚነት ስለሚኖረው ጠቀሜታ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑም በስምምነቱ ላይ ተመልክቷል፡፡
ምንጭ፦ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት