የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ከቱርክ መንግስት ጋር በሕግና ተያያዥ ጉዳዮች ትብብር ዙሪያ መከረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዓለምአንተ አግደዉ የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሁለትዮሽ የሕግ ትብብር ጉዳዮች ላይ ለመምከር ቱርክ አንካራ ገብቷል፡፡
ለልዑካን ቡድኑ የቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ያኩፕ ሞጉል እና ሌሎች የቱርክ ፍትሕ እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ደማቅ አቀባበል መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡
የልዑካን ቡድኑ በቱርክ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን እና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር አደም መሀመድ በተገኙበት ከቱርክ መንግስት ጋር በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸዉ የሕግና ተያያዥ ጉዳዮች ትብብር ዙሪያ ምክክር አድርጓል፡፡
በቀጣይ ቀናትም በኢትዮጵያ እና በቱርክ መንግስት መካከል በሕግ ትብብር ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡