Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ6 ነጥብ 6 በመቶ የሚያድግ መሆኑን ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመላከተ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ በ6 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያድግ ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም አመላካች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ተናገሩ።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ አለም አቀፋዊ ጫናዎችና የአገር ውስጥ ጉዳዮች ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተና እንደነበርም ነው የጠቆሙት ።
የኢትዮጵያ የ9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ በተገኙበት ተገምግሟል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ ያለፉት 9 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን÷ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖም በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው ባላፉት 9 ወራት በተለይ በግብርና፣ ወጪ ንግድና አገልግሎት ዘርፎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
በግብርና መስክ 336 ሚሊየን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው÷ ከዚህም ውስጥ በበጋ መስኖ ልማት 25 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል ነው ያሉት፡፡
ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከውጪ ንግድ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጸው÷ ከአገልግሎት ዘርፍም 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን መናገራችውን ኢዜአ ዘግቧል።
በሌሎች ዘርፎች ላይም የተሻለ አፈጻጸም መኖሩን ጠቅሰው÷ ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ችግሮችን ተቋቁሞ በ6 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያድግ ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
ነገር ግን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በአገር ውስጥ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ በማድረግ ማክሮ ኢኮኖሚውን በብርቱ መፈተኑን አብራርተዋል።
ለአብነትም ማዳበሪያ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ቶን ከነበረበት የ250 ዶላር ዋጋ አሁን ላይ ወደ 1 ሺህ 300 ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የስንዴና የዘይት ዋጋ በጥርና መጋቢት ወራት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 65 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ገልጸው÷ ይህም በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ያዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትን ለመቋቋም የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዜጎች ሰላምና ጸጥታ በማስከበር የድርሻቸውን በመወጣት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.