ካፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ እንዲያካሂድ ወሰነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) የአፍሪካ እግርኳስ ፌዴሬሽን (ካፍ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ እንዲያካሂድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ከስድስት ወራት በፊት ‘‘ኢትዮጵያ በሜዳዋ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል እና የካፍን ደረጃ የሚያሟላ ስታዲየም የላትም’’ በሚል በሜዳዋ ማድረግ የሚገባትን ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ስታደርግ መቆየቷ ይታወሳል።
ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላም በስታዲየሞቹ የተሻሻለ ነገር ባለመኖሩ ምክንያት ኢትዮጵያ በድጋሚ በሜዳዋ እንዳትጫወት ካፍ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
በዚህ ወር መገባደጃ ላይ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳዉው እንዲጫወት እና የካፍ አመራሮችን ዝቅተኛ መስፈርት እንኳን ለማሟላት ርብርብ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ መቅረቱ ታዉቋል።
በዚህም የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን(ካፍ) ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በላከው ደብዳቤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያን በሜዳዋ እንድትጫወት ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን አሳውቋል፡፡
በውሳኔው መሰረትም እስከ ግንቦት 4 ድረስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሜዳው ውጭ የሚጫወትበትን ሜዳ ይፋ እንዲያደርግ ካፍ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡