Fana: At a Speed of Life!

ገንዘብ ሚኒስቴር የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የፌዴራል እና የክልሎች የፋይናንስ አስተዳደር የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ወጪ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ሽመልስ÷ በሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶችና በክልል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ እንዲደረግ በሚኒስቴሩ የወጣውን የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን ተግባራዊ በማያደርጉ ተቋማት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያ ቁጥር 51/2010 ተግባራዊ መደረግ ዘመናዊ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፥ ከወረዳ ጀምሮ ባሉ መዋቅሮች ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመልካም አስተዳደር መጎልበት እንደ አንድ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት ተግባራዊ መደረጉ የዜጎች የመሰረታዊ አገልግሎቶች ቅድመ ፍላጎት በዕቅድ እንዲካተት በማድረግ፣ በበጀት አመዳደብና በወጪ አስተዳደር ተሳትፎ፣ በመንግስት ግዥ አፈፃፀምና የኦዲት ግኝት መረጃዎችን ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ ግጭትና አለመረጋጋት፣ የፋይናንስ ግልፅነትና ተጠያቂነት መመሪያን በቁርጠኝነት ተግባራዊ ለማድረግ ያላስቻሉ ችግሮች እንደነበሩ መገለጹን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.