Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሸ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትና አርአያ የሆነ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ቻይና ከግማሸ ምዕተ-ዓመት በላይ ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ያካበቱና ለደቡብ-ደቡብ የትብብር ማዕቀፍ አርአያ የሆነ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ተናገሩ።

በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ይህን የተናገሩት፥ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲና የደቡብ ቻይና ግብርና ዩኒቨርሲቲ ለወደፊት በጋራ ለመስራት በሚያስችሏቸው የትብብር መስኮች ዙሪያ የመጀመሪያ ውይይታቸውን በዌቢና ባካሄዱበት ውቅት ነው።

ቤጂንግ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስተባባሪነት በተዘጋጀው ውይይት ላይ የተሳተፉት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የኢትዮጵያ መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ የሚገኝ ገልጸዋል።

የቻይና መንግስት በተለይ በአፍሪካ ቻይና የትብብር ማዕቀፍ ትኩረት ከሰጣቸው ግቦች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲሁም የድህነት ቅነሳና የግብርና ልማት ፕሮግራሞች ዋነኞቹ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በዚህም የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲና የደቡብ ቻይና ግብርና ዩኒቨርሲቲ የሚያደርጉት ትብብር ኢትዮጵያ የተቀናጀ የግብርና አሰራርን በመከተልና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከድህነት ለመውጣትና በምግብ አቅርቦት ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆን ለምታደርገው ጥረት መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።

አክለውም ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሰው ሀብት ልማት፣ በቴክኖሎጂ በታገዘ የተቀናጀ የእርሻ ስራ፣ በትምህርትና ስልጠና፣ በተማሪዎችና በመምህራን ልውውጥ፣ በአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ እንዲሁም በቆሻሻ ውሀ ህክምና ዘርፎች በጋራ ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኤምባሲው ለትብብሩ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማንኛውም ጊዜ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የደቡብ ቻይና ግብርና ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ሺው ሮንግሊያንግ በበኩላቸው ፥ ኤምባሲው ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች ለማቀራረብና በጋር ተባብረው እንዲሰሩ ለማስቻል ላደረገው ከፍተኛ ጥረት አመስግነው፥ ዩኒቨርሲቲያቸው ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር በተጠቀሱት የትብብር መስኮች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛና ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲያቸው ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች፣ መምህራንና የግብርና ባለሙያዎች ተጨማሪ የነፃ የትምህርትና የስልጠና እድሎችን የሚያመቻች መሆኑን መግለጻቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.