Fana: At a Speed of Life!

የቆየውን የሃይማኖቶች መቻቻልና መከባበር አጠናክሮ መቀጠል ይገባል – ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቆየውን የሃይማኖቶች መቻቻልና መከባበር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ገለጹ፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ ከጎንደር ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት÷ በእስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች መካከል ያለው አንድነትና መከባበር በቀጣይም በተጠናከረ መንገድ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በሃይማኖት ተከታዮች መካከል እውነተኛ መተሳሰብ ሊኖር እንደሚገባ ገልጸው÷ ወጣቶች የሃይማኖት አባቶችን ምክር በመስማት ራሳቸውን ከጥፋት መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
የየትኛውም ሃይማኖት ተቋማት የአክራሪዎች መደበቂያ መሆን እንደሌለባቸው እና መንግስትም ሕግ የማስከበር ስራውን በትኩረት መከወን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሲካሄድ የቆየው ውይይት ባለ አምስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት እና በጋራ መግባባት ተጠናቋል።
በአቋም መግለጫው÷ በጎንደር ከተማ የተደረገው ድርጊት ሁለቱንም ሃይማኖቶች የማይወክልና ድርጊቱም የተወገዘ መሆኑን አመልክቶ፥ እና ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ለመከባበርና ለተጠናከረ አንድነት በጋራ እንደሚቆሙ ጠይቋል፡፡
በድርጊቱ የተጎዱ ወገኖችን የመደገፍና የማቋቋም ስራ እንደሚከናወን እና አጥፊዎችን መንግስት ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም የአቋም መግለጫው አመልክቷል፡፡
በምናለ አየነው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.