Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል ሲካሄድ የቆየው የሸዋል ኢድ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ላለፉት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው የሸዋል ኢድ በዓል ተጠናቋል።

በበዓሉ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የተገኙት የዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሃመድ ኢድሪስ እንዳሉት ፥ የሐረር ስልጣኔ አሻራ በኢትዮጵያ ስልጣኔ ላይ ጉልህ ሚና አበርክቷል።

የባለ ብዙ ታሪክና ቅርስ ባለቤት የሆነችው ሐረር ትልቅ መገለጫና መነሻ ያላት መሆኗን ከሚያሳዩ እሴቶች መካከል የሸዋል ኢድ በዓል አንዱ መሆኑን አውስተዋል።

የሐረሪ ክልል ባህል፥ ቅርስና እሴቶች እንዲጠናከሩና እንዲተዋወቁ ከማድረግ አንፃርም የዳያስፖራ ኤጀንሲ በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በውጭ ሀገር የሚገኙ የሐረሪ ተወላጆችና መላው ኢትዮጵያውያን አደረጃጀታቸውን በማጠናከር ለሀገሪቱ ሁለተናዊ ለውጥ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

በሸዋል ኢድ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ የሸዋል ኢድን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት ማስመዝገብ ስለሚኖረው ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ እንዲሁም በሐረሪ ‘‘በጌይሞት’’ በመባል ስለሚጠራው የአለላ ስፌት የእደ ጥበብ ውጤት ላይ የመለያ ምልክት ለማዘጋጀት የተደረገ የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የሸዋል ኢድ ከሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በሐረሪ ክልል ሲከበር ቆይቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.