Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሐቅ በቅጡ በመረዳት እና አምኖ በመቀበል ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ማስቀጠል አለብን – አፈጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ነባራዊ ሐቅ በቅጡ በመረዳት እና አምኖ በመቀበል፣ በንግግር እና በመግባባት፣ ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ማስቀጠል አለብን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎ ተናገሩ።

“ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል መሪ ሐሳብ በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደውና ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ፥ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሐቅ በቅጡ በመረዳት ስለ ኢትዮጵያ ሰላም፣ ዕድገት፣ አብሮነት እና መቻቻል በጋራ መሥራት የግድ ይለናል ብለዋል።

“ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በጋራ ለመሻገር፣ ዕድሎችን ለመጠቀም እና ተስፋዎቻችን ፍሬ እንዲኖራቸው ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባልያሉት አፈጉባኤው፥ ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የፈተና ጊዜያት አንጸባራቂ ድሎች መመዝገባቸውን አውስተዋል።

ስለሆነም አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት፤ ኢትዮጵያን ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር ይጠበቅብናል ሲሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ፤ ሰላም እና አንድነቷን በማስጠበቅ ረዥም ዘመን ያስቆጠረ የሀገረ-መንግሥት ታሪክ ባለቤት መሆኗን ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሚገባም ጠቁመው፥ የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ሰላም እና አንድነት የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ በበኩላቸው፥ ሌሎች ሀገሮችም የገጠሟቸውን ችግሮች የፈቱባቸው የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ለኢትዮጵያ የሚመቸውን በመምረጥ ከችግር ለመውጣት መሥራት አለበን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያለፈቻቸውን ፈተናዎችና ያስመዘገበቻቸውን ድሎች መነሻ በማድርግ ወደፊት የተሻሉ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ የውይይት መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውንም ነው አፈጉባኤው ያመለከቱት።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ እና ዓለም-ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሬሳ፥ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታዎችና መገለጫዎች በአግባቡ በመረዳት፣ በመተባበር፣ በመተጋገዝ፣ በመቻቻል እና ተነጋግሮ ችግሮችን በመፍታት፤ የሀገርን ሕልውና ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አብርሃም አለኽኝ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያን ለህዝቦቿ መኖሪያ የተመቸች ሀገር ለማድረግ በጋራ እንሥራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች እንዲባባሱ እና እንዲስፋፉ ጥረት የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን አመላክተዋል።

ከኢትዮጵያ ቂም እና ጥላቻ እንዲሁም ቁርሾ ተወግዶ አብሮነት እና የጋራ ሀገር መገንባትን ዓላማ አድርጎ መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ ታገሰ ጫፎ እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በመድረኩ እየተሳተፉ መሆናቸውን ከፓርላማ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.