የሀገር ውስጥ ዜና

ኢ/ር ታከለ ኡማ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

By Meseret Awoke

May 10, 2022

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡

ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፥ የማዕድን ዘርፋችን ከወቅቱ የዓለም ሁኔታ ጋር እንዲራመድና ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲያድግ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር መስራትን ይጠይቃል ነው ያሉት።

በዛሬው እለትም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሆኑት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ አፍሪካ ልማት ባንክ፣ የኔዘርላንድ ልማት ባንክና የፈረንሳይ ልማት ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል ሚኒስትሩ፡፡

ውይይቱም የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝ ለማድረግ እንደሆነም ነው የገለጹት።

በተለይም የጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተቋማቱ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።