Fana: At a Speed of Life!

ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በሃይማኖትና በብሔር ሽፋን ኢትዮጵያውያንን ችግር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች በሃይማኖትና በብሔር አማካይነት ኢትዮጵያውያንን ችግር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ʺበሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ የፀጥታ አባላት እውቅናና የማዕረግ ዕድገት ዛሬ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተሰጥቷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳስታወቁት ፥ ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ለመጣል የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች እየሴሩ ይገኛሉ።

ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎቹ በሃይማኖትና በብሔር አማካኝነት ኢትዮጵያውያንን ችግር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በመሆኑም የተደቀነብንን አደጋ በመረዳትና ይህን አጀንዳ ለመመከት ህዝቡ አንድነቱን መጠበቅ አለበት ብለዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የፈፀመው ሀገር ለማፍረስ በማለም መሆኑን አስታውሰው ፥ በመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች የፀና ተጋድሎ ሴራው መክሸፉን አስረድተዋል።

“ጦርነትን የማንፈልገው የሚያስከትለውን ጉዳትና የሚያስከፍለውን ዋጋ ስለምንገነዘብ ነው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፥ አሸባሪው ቡድን ከጥፋት ድርጊቱ እንዲታቀብ አሳስበዋል።

የትግራይ ህዝብና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቡድኑ ከጥፋቱ እንዲመለስ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተው ፥ መንግስት ማንኛውንም ትንኮሳ ለመመከት ሙሉ አቅምና ዝግጁነት እንዳለው ጠቁመዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የወጠነውን ሴራ በተደራጀ አግባብ በማክሸፍ የፀጥታ ሃይሉና ህዝብ ያበረከተው ሚና በታሪክ ሲወሳ የሚኖር ነው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ናቸው።

የክልሉ የፀጥታ ሃይል ከፌዴራልና ሌሎች ክልሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተባበር ወራሪውንና አሸባሪውን ህወሓት ድባቅ በመምታት ሴራውን ማክሸፍ እንደተቻለ አስታውሰዋል።

የዛሬው እውቅናና የማዕረግ እድገት መስጠት መርሐ ግብር የፀጥታ ኃይሉን ሞራል በማነሳሳት አሸባሪው ህውሃት ሊፈፅም ያቀደውን ዳግም ወረራ ለማምከን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ቡድኑ ለዘመናት ከትግራይ ህዝብ ጋር ተዋልዶና ተዛምዶ በኖረው የአማራ ህዝብ ላይ ዘግናኝ ግፍና በደል መፈፀሙንም ነው አቶ ደመቀ ያወሱት ።

የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው ፥ በህልውና ዘመቻው ተጋድሎ ለፈፀሙ ጀግኖችንና የጀግና ቤተሰቦችን እውቅና መሰጠቱ ሰራዊቱን ለላቀ ግዳጅ እንደሚያዘጋጀው ተናግረዋል።

የማዕረግ ዕድገት የተሰጣቸው አመራሮችና ተዋጊዎች የተሰጣቸውን ግዳጅ በጥብቅ ዲስፕሊን በመምራትና በመፈፀም ለተገኘው ድል የላቀ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው ሲሉም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.