ኢራን በሳይንስ ዘርፍ ያላትን ልምድና ዕውቀት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ሀገራት ማካፈል እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢራን የተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ፈር-ቀዳጅ እንደሆነች እና ያላትን ልምድ እና ዕውቀት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ሀገራት ለማካፈል ደስተኛ ስለመሆኗ አምባሳደር ሳማድ አሊ ተናግረዋል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ በኢትዮጵያ ከኢራን አምባሳደር ሳማድ አሊ ላኪዛዴህ ጋር የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ምክክርን ጨምሮ፤ በሁሉም መስክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችላቸው መንገዶች መክረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ ፈተናን ወደ መልካም አጋጣሚ ስለመቀየር ከኢራን ተምራለች” ሲሉም ዶክተር ዲማ ተናግረዋል።
ኢራን በታሪኳ የተለያዩ የውጭ ተጽዕኖዎችን ተቋቁማ ለስኬት እንደበቃች ሁሉ፤ ኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየገጠማት ያለውን የውጭ ተጽዕኖ መቋቋም ትችል ዘንድ ከኢራን ብዙ እንደምትማር ዶክተር ዲማ ነገዎ ለአምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡
ኢራን እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ1943 ዓ.ም. ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ መስኮች፤ በኢኮኖሚ፣ በባሕል፣ በግብርና እና ኢንዱስትሪ እንዲሁም የሳይንስ ዘርፎች የረጅም ዘመን ትብብር እንደነበራቸው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አስታውሰዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ከሃያ በላይ የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን አምባሳደሩ አስታውሰው ፥ ኢራን ለማንኛውም ቀጣይ ትብብር ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ኢራን የተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች ፈር-ቀዳጅ እንደሆነች እና ያላትን ልምድ እና ዕውቀት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወዳጅ ሀገራት ለማካፈል ደስተኛ ስለመሆኗም፤ አምባሳደር ሳማድ አሊ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም ፥ ለበርካታ ዓመታት ተዘግቶ የቆየው የቴህራን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከፍቶ ሥራውን የሚጀምርበት ሁኔታ እንዲኖር ቋሚ ኮሚቴው ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በበኩላቸው ፥ የኤምባሲው ሥራ መጀመር የፓርላማ ዲፕሎማሲን ጨምሮ ሁለቱ ሀገራት ለሚያደርጉት ትብብር ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማቶችን ቁጥር መመጠን ኢትዮጵያ በቅርቡ ያደረገችው ሪፎርም አንዱ አካል እንደሆነም እግረ-መንገዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እና ኢትዮጵያ ከኢራን ጋር ያላት ትብብር በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ከመሆኑም ባሻገር፤ በቀጣይም ሁለቱ ሀገራት በወዳጅነት አብረው መቀጠል ስለሚኖርባቸው፤ በቴህራን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሥራውን ይቀጥል ዘንድ ቋሚ ኮሚቴው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሰራ ዶክተር ዲማ ገልጸዋል፡፡