Fana: At a Speed of Life!

ድርጅቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከደንበኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያየ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከደንበኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ የመንግስትና የግል አስመጭዎች፣ ላኪዎች፣ አምራችና የልዩ ድጋፍ ተጠቃሚዎች፣ ትራንስፖርተሮች እና ትራንዚተሮች (የጉምሩክ አስተላላፊዎች) እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የኢባትሎአድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ ባድረጉት ንግግር፥ በአሰራር ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን መግለጻቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ድርጅቱ ለደንበኞች በሚሰጣቸው የባሕር እና የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም በወደብና ተርሚናሎች አገልግሎት በጥንካሬ የሚገለጹ መልካም የስራ ሁኔታዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የተገለጸ ሲሆን ፥ በአሰራር ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችም ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

እንደ ችግር ከተነሱት መካከል አልፎ አልፎ የሚያጋጠሙ የሲስተም መቆራረጥ፣ የኮንቴየነር ማስያዣ መጨመር፣ የኮንቴይነር ተመላሽ ክፍያ መዘግየት፣ በሞጆ ወደብና ተርሚናል ከጉልበት ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ፣ እንዲሁም የዌቨር ይፈቀድልን ጥያቄ በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡

ለተነሱ ጥያቄና አስተያየቶችም የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ መሪዎች ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ኢባትሎአድ የደንበኞቹን ጥያቄ ለመመለስና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትጋት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.