Fana: At a Speed of Life!

የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍ ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍ እንዲቻል ተመጣጣኝ የአገልግሎት ክፍያ ጥናት እንዲደረግ አቅጣጫ ተሰጠ፡፡

የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ መስሪያ ቤቶች የ2015 ዓመት የበጀት እቅዳቸውን ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲያቀርቡ የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍና ለማጠናከር እንዲቻል አቅም ያላቸው ታካሚዎች ከአገልግሎቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

የበጀት ሰሚ መርሐ ግብሩን የመሩት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ፥ መንግስት የጤናውን ዘርፍ በበጀት ለመደገፍ አቅም በፈቀደ መጠን ጥረት የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።

የጤና ተቋማት ለሚሰጡት አገልግሎት ‘‘በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ነው የምንቀበለው’’ የሚለውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ አቅም ያለውንና የሌለውን በመለየት አቅም ያላቸው ታካሚዎች ከአገልግሎቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነና ተገቢ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ጥናት ተጠንቶ እንዲቀርብ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

የጤና መድህን ዋስትና ለዘላቂ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ስትርቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር እዮብ ጠቁመው ፥ የጤና ተቋማት አገልግሎት በመስጠት የሚያገኙትን የውስጥ ገቢ የሀገሪቱ የፋይናነስ አስተዳደር ደንብ በሚፈቅደው መሰረት በአግባቡና ከሙስና በጸዳ መልኩ ጥቅም ላይ የሚያውሉበት ስልት እንዲነደፍም ማመለካታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የጤና ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙት 11 ተጠሪ ተቋማት ለመጪው በጀት ዓመት ያቀረቡት የበጀት እቅድ ገንዘብ ሚኒስቴር ካስቀመጠው የበጀት ጣሪያ በላይ በመሆኑ፥ ሚኒሰቴሩና ተቋማቱ በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በተቀመጠላቸው የበጀት ጣሪያ መሰረት የበጀት እቅዳቸውን አስተካከለው እንዲያቀርቡም መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.