Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችና ሚኒስትሮች ባሕር ዳር ገቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችና ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው በሕግ ማስከበርና በኅልውና ዘመቻ ለተሳተፉ የጸጥታ አካላት የዕውቅና መርኃ ግብር ላይ ለመሳተፍ ባሕር ዳር ገብተዋል።

ለርእሳነ መሥተዳድሮችና ሚኒስትሮች÷ የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበርና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር በላይ ዘለቀ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር የጥፋት መንገዱን አክሽፈዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ባዘጋጀው የምሥጋናና የእውቅና መርኃ ግብር ለጸጥታ አካላት፣ ግለሰቦችና ተቋማት የዕውቅና መርኃ ግብሩ ትናንት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ዛሬም በሕግ ማስከበርና በኅልውና ዘመቻ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ መከላከያ፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ፖሊስ፣ ፋኖ፣ ሚሊሻና የክተት ጥሪ ተሳታፊ የሕዝብ ኀይል ዕውቅና ይሰጣል።

ከሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ጋር ሲፋለሙ በጀግንነት የተሰውትም ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በክብር ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በዘመቻው የተሳተፉ ተቋማት፣ ባለሐብቶች፣ የብዙኀን መገናኛዎችና ሌሎች አደረጃጀቶችም ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የክልል ርእሳነ መሥተዳድሮችም ኢትዮጵያን ለማዳን በተደረገው ዘመቻ ላደረጉት አስተዋጽኦ ዕውቅና ይሰጣቸዋል መባሉን አሚኮ ዘቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.