Fana: At a Speed of Life!

19ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 19ኛው የኢኖቬሽን አፍሪካ ዲጂታል ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ጉባኤው የዲጂታል ይዘትና አገልግሎት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ነው እየተካሄደ ያለው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የባህልና የቋንቋ ብዝሃነት ያላቸው ሀገራት የዲጂታል ይዘቶችና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል አካታችነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያም በዲጂታል 2025 ስትራቴጂዋ ላይ አካባቢያዊ የዲጂታል ይዘት እና አገልግሎትን አካታ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፥ የሀገር ውስጥ የይዘት አቅራቢዎች፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች እና የዓለም አቀፍ የዘርፉ ተዋናዮች የዲጂታል ይዘቶችን ዘላቂነት በማረጋገጥ የማይተካ ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ከግብ ለማድረስ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የ5ኛ ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት ጅማሮ የዲጂታል አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
በጉባኤው ላይ ከ30 በላይ ሀገራት የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ኩባንያዎች እና የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪዎች እየተሳተፉ ነው።
በፈቲያ አብደላ፤ ተጨማሪ መረጃ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.