Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን በጋራ የምንቆምና ህልውናችንን የምናስከብር ነን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም እንኳ እንደቀደምት አባቶቻችን ሁሉ በኢትዮጵያ ተግባብተን በጋራ የምንቆምና ህልውናችንን የምናስከብር ነን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው በህልውና ዘመቻው የላቀ አስተዋፅኦ ላደረጉ የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ “ጠላቶች ሸንበቆ አንድ መሆኑን መገንዘብ ስላልቻሉ ኢትዮጵን በዘር ፣ በሃይማኖት፣ በባህልና ቋንቋ የተከፋፈለች ናት ይላሉ፤ ቀደምት አባቶቻችን ግን ከቋንቋ እና ባህል ይልቅ በኢትዮጵያ ተግባብተው ነፃይቱን ሀገር አስረክበውናል” ብለዋል ።

ዛሬም በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያለን ቢሆንም እንኳን በጋራ የምንቆምና ህልውናችንን የምናስከብር ነን ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ጀግኖች በችግር ጊዜና እና በክፋ ቀን፣ ደማቸውን አፍስሰው ፣ አጥንታቸውን ከስክሰውና ህይወታቸውን ሰውተው ነፃነታችንን የሚሰጡን ልዩ ሰዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እነሱን በማስታወስ እና በማወደስ አርአያ እንዲሆኑ ማድረግ መታደል መሆኑም ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ የፀጥታ አስከባሪ አካላት ፣ የፋኖ አባላትና አመራሮች ፣ የተሰው ጀግኖች ቤተሰቦች ፣ ባለሀብቶች፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና አመራሮች እንዲሁም የክልል መንግስታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ምስጋና እና እውቅናን ተሰጥቷቸዋል ።

የዛሬው የእውቅናና የምስጋና እንዲሁም የሽልማት መርሐ ግብር ሀገራቸውን ለሚወዱ እና ዋጋ ለከፈሉት ሁሉ ይሁንልን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ።

በፀጋዬ ወንድወሰን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.