Fana: At a Speed of Life!

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመርታ ሰዋሰው ከአውሮፓ ህብረት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመርታ ሰዋሰው ከአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ ትብብር የአፍሪካ ዳይሬክተር ሳንድራ ክራመር እና በአውሮፓ ህብረት የውጪ አገልግሎት የአፍሪካ ዳይሬክተር ሪታ ላራ ጋር በብራሰልስ ተወያይተዋል፡፡
 
በውይይታቸውም ሚኒስትር ዴኤታዋ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል አሁን ላይ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ዙሪያ ለአመራሮቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
በዚህም መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን ግጭት ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲመረመሩ፣ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲዳረስ፣ በግጭት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ እንዲሁም አገራዊ ምክክሩ የደረሰበትን ሂደት አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ድርቅ እና የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናርን ተከትሎ በተፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
ለእነዚህ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀትም የኢትዮጵያ መንግስት ከሚመለከታቸው የልማት አጋር አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡።
 
የአውሮፓ ህብረት አመራሮች በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች ማድነቃቸውን በቤልጂዬም ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
በግጭቱ ሳቢያ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊው የሰብዓዊ እርዳታ እንዲዳረስ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.