Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ መልክተኛ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ መልክተኛ ፊሊፕ ፋርማን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
 
በውይይታቸውም አምባሳደር ሬድዋን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለልዩ መልክተኛው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
 
የአገር ውስጥ ጉዳዮችን ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሄድ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻልበት ሰፊ እድል መኖሩን የገለጹት አምባሳደር ሬደዋን÷ የፌደራል መንግስቱ በአገሪቱ ሰላም ለማስፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
 
የፌደራል መንግስቱ በአገሪቱ ሰላም ለማሰፈን በርካታ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸው÷ መንግስት ለወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔና ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ሊያደንቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
 
የትግራይ ሕዝብ ህዝባችን እንደመሆኑ እርዳታ በወቅቱ መድረስ ስለሚገባ ህወሓት አሁንም ተቆጣጥሯቸው የሚገኙ አንዳንድ የአፋር አካባቢዎችን ለቆ እንዲወጣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ግፊት ማድረግ እንዳለበም አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
የእንግሊዙ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ መልክተኛ የሆኑትን ፊሊፕ ፋርማን በበኩላቸው÷ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ውስብስብ የሆነ የፍላጎቶች ግጭት መኖሩንና ኢትዮጵያ ይህንን የጋራ ፈተና በመታገል ረገድ ትልቅሚና መጫወት እንደሚኖርባት አንስተዋል፡፡
 
የኢትዮጵያ መንግሰት በሰሜኑ አካባቢ የነበረውን ግጭትለማስቆም የተኩስ ማቆምና ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲገባ የወሰደውን እርምጃም አድንቀዋል፡፡
 
ልዩ መልክተኛው የሰብዓዊ እርዳታው ከትግራይ ክልል ባሻገር ለአፋርና አማራ ክልሎች የሚደርስበት እድል መኖር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለቸውና ይህንንም የሰላም ሂደት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.