Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 75 አመራርና ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 75 አመራርና ሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
 
በአገልግሎቱ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር አቶ ህብረወርቅ ይመኑ÷ተቋሙ ባለፉት 9 ወራት ከተለያዩ አካላት የቀረቡ 97 ጥቆማዎች እና 163 አቤቱታዎችን ተቀብሎ የማጣራ ስራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
 
በዚህም የሥነ-ምግባር ጥሰት በፈፀሙ 75 አመራርና ሰራተኞች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መውሰዱን እና ቀሪ 87 የሚሆኑት ጉዳያቸው በስነ ምግበር በመታየት ሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት፡፡
 
አስተዳደራዊ እርምጃው የተወሰደው በተቋሙ ህብረት ስምምነት እና በማኔጅመንት መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ÷የገንዘብ ቅጣት፣ ከኃላፊነት ቦታ ማንሳት እንዲሁም እስከ ስራ ስንብት የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል፡፡
 
አብዛኛው የተቋሙ ሰራተኛ ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት የበኩሉን ጥረት እያደረገ ቢሆንም ጥቂቶች በህገ-ወጥ መንገድ አገልግሎቱን ለማግኘት ከሚፈልጉ አካላትና ደላሎች ጋር በመሆን ብልሹ አሰራር የሚፈጽሙ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
 
በህገ-ወጥ መንገድ ቆጣሪ ማስገባት፣ ቆጣሪ ለማስገባት በሚደረገው ሂደት ጉቦ መጠየቅ፣ ደንበኛን በአግባቡ አለማስተናገድ፣ ያለበቂ ምክንያት ስራን ማዘግየትና ደንበኛን ማጉላላት፣ በአስቸኳይ ጥገና ስራ ደንበኞች ገንዘብ በማዋጣት እንዲከፍሉ ማስገደድ፣ ያለደረሰኝ የቆጣሪ ማስገቢያ ክፍያ መቀበል እና የመሳሰሉት በተደረገ ማጣራት ስራ የተገኙ የብልሹ አሰራር መገለጫዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
 
ተቋሙ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ተቋሙ የተለያዩ የቅሬታ ማስተናገጃ ስርዓት መዘርጋቱን የገለፁት አቶ ህብረወርቅ÷ ደንበኞች በተዘረጉ የቅሬታ ማቅረቢያ ስርዓቶች ቅሬታቸውን፣ ጥቆማቸውን እና ሃሳባቸውን ማቅረብ ይችላሉ ማለታቸውን ከአገልግሎቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.