በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች በተጨባጭ የኀብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ሊሆኑ ይገባል-ዶ/ር መኩሪያ ኃይሌ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች በተጨባጭ የኀብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ሊሆኑ እንደሚገባ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሰባተኛውን ዓመታዊ የምርምር ጉባኤ “የህዝብ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለውጥ እና ልማት” በሚል መሪ ሃሳብ ባካሄደበት ወቅት ነው።
የጉባኤው ዋነኛ ዓላማ በአገልግሎት ሰጪተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ለፖሊሲ ግብዓት ማቅረብ መሆኑ ተመላክቷል።
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ የምርምር ስራዎች እሴት የሚጨምሩና የኀብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በጥናትና ምርምር መስክ ለሚሰማሩ ወጣቶች ተጨማሪ ግብዓት የሚሰጡ ሊሆን እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው የምርመር ዘርፍ ትምህርት ክፍል ከሰባት ዓመት በፊት ማቋቋሙን አስታውሰዋል።
በዚህም የሲቪል ሰርቪስ ችግሮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን በማከናወን ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ጥናቶቹ የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ለሚከናወኑ ተግባራት እንደግብዓት እየተወሰዱ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በዩንቨርሲቲው በምርምር ስራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ዶክተር ታድዮስ ሜንታ እና ዶክተር አብርሀም ሞገስ፤ በተለያዩ የትምህርት ተቋማት በርካታ ጥናቶች ቢደረጉም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑበት እድል ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ በዩንቨርሲቲው የሚጠኑ ጥናቶችን ለሚመለከታቸው ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በመላክ ለችግር ፈቺ የፖሊሲ አማራጮች ግብዓት እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የጥናት ውጤቶች ከመደርደሪያ ወርደው የኀብረተሰቡን ችግር ለመፍታት ገቢራዊ ሊደረጉ ይገባል ነው ያሉት፡፡